1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«328 ዋሻዎች አግኝቼያለሁ» የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2016

የዋሻ ተመራማሪ የሆነው ወጣት ናስር አህመድ በስሙ ናሲኦል የሚለው ዋሻ ከተሰየመ አራት አመት ሆነው። ዋሻው ኢትዮጵያ ውስጥ ካገኛቸው በውበቱ ልዩ የሆነዉ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ወራት ለሀገር ጎብኝዎች ክፍት እንደሚሆን ገልፆልናል።

https://p.dw.com/p/4fR43
የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ
የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድምስል N. Ahmed

«328 ዋሻዎች አግኝቼያለሁ» የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ

«ለሚያጨስ፣  አልኮል ለሚጠጣ ወይም ጭለማ ለሚፈራ ሰው የዋሻ ተመራማሪ መሆን ከባድ ነው» ይላል የዛሬው  እንዳችን! ጤና ይስጥልኝ ውድ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች!  የ 29 ዓመቱ  ናስር አህመድ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው ቃለ መጠይቆች ሀሳቡን በደንብ መግለፅ እንዲችል በኦሮምኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንደነበሩ ነግሮናል። ዛሬ ደግሞ በአማርኛ የመጀመሪያውን ቃለ መጠይቅ ከእኛ ጋር አድርጓል። 

ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ዋሻዎች

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ዋሻ በማጥናት የመጀመሪያው ባለሙያ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ናስር አህመድ ወደዚህ ሙያ ከገባ 10 ዓመት አለፈው። በእነዚህ አመታት ያገኛቸው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ዋሻዎች ከ400 በላይ ደርሰዋል።  « እስካሁን ወደ 328 የተፈጥሮ ዋሻዎች እና ሰው ሰራሽ የሆኑ 82 ዋሻዎች አግኝቻለሁ። ከዚህም ሌላ የዋሻ ድንጋዮች 128 የሚሆኑ አግቻለሁ።» 

የናሲኦል ዋሻ ለምን እንዲህ ማራኪ ሆነ? 

ናስር አሁንም ልዩ የሚለው ዋሻ ከአራት ዓመት በፊት በስሙ የተሰየመው የናሲኦል ዋሻ ነው።  « 328ቱ ዋሻዎች ውስጥ የሚገኙ ማራኪ ነገሮች በዚህ በአንድ ዋሻ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ዋሻ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን መልካበሎ ወረዳ ይገኛል። መግቢያው ላይ በጣም ጠባብ ነው። ነገር ግን ከ 31 ሜትር በኋላ ወደ 200 ሜትር ስፋት አለው። » ይህ ብቻ አይደለም።  ይህንንም ቦታ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ናስር ይናገራል። « ሶስት ወር ሙሉ መንገድ እየተሰራ ነበር። አሁን ዋሻው ጋር ለመድረስ 6,5 ኪ ሜትር መንገድ ሰርተን መኪና ዋሻው ድረስ ይደርሳል። መገዱን ጨርሰናል። የሚቀረው ዋሻ ውስጥ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ናቸው።  » ይላል ናስር ። በአራት ወራት ውስጥ ያልቃል የሚል እምነትም አለው።

ዋሻ የሚበዛባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች

ዋሻ የሚበዛባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ምስራቅ ሀረርጌ ፣ ምዕራብ ባሌ እና አርሲ አካባቢዎች እንደሆኑ የነገረን የዋሻ ተመራማሪ ፣ የዋሻዎቹ አይነት እና ውበትም እንደ መሬት አቀማመጡ እንደሚለያይ ያስረዳል።  « ብዙ ጊዜ ዋሻ ያለው ላምስቶን የሚገኝበት ቦታ ነው።  ይህም ያለው ወደ ምስራቅ ሀረርጌ ፣ ምዕራብ ባሌ እና አርሲ አካባቢዎች ነው ላምስቶን የተፈጠረው። ሌሎች ቦታዎችም ግን አሉ። »

የናሲኦል ዋሻ መግቢያ
«የናሲኦል ዋሻ መግቢያው ላይ በጣም ጠባብ ነው። ነገር ግን ከ 31 ሜትር በኋላ ወደ 200 ሜትር ስፋት አለው።»ምስል N. Ahmed

በአምስት የተከፈሉት የዋሻ አይነቶች

አብዛኞቹ የአውሮፓ ዋሻዎች የቱሪዝም መዳረሻ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው የሚለው ናስር  ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የተገኙትን በአምስት ዘርፎች ከፍሎ ይተነትናል። « የመጀመሪያው  የሜዲሲን ዋሻ የምንለው ነው። ሲቀጥል ኢንዱስትሪያል፣ የማዕድን ፣ የፊዞቴራፒ እና የቱሪዝም ዋሻዎች ተብለው 328ቱ ተለይተዋል። » በጣም ቆንጆ የሚባሉት ግን የናሲኦል እና የኦሮሞ ዋሻዎች ናቸው» ይላል የዋሻ ተመራማሪው።
ስለ ዋሻ ጥናት የሚያደርገው  እና ስፒሊዮሎጂ የሚለው ሙያ  ትምህርት እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ አፍሪቃ ውስጥም የለም የሚለው ናስር ይህንን ከልጅነቱ አንስቶ  ፍቅር ያሳደረበትን ሙያ ለመማር ወደ ፈረንሳይ ከመሄዱ በፊት በቅድሚያ በኦንላይን ጣሊያን ሀገር ነበር ለሶስት አመታት የተማረው።  ከዛም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ኦሮምያ ባህል እና ቱሪዝም ተቀጥሮ ከሰራ በኋላ ፈረንሳይ ሀገር ለሁለት አመት ትምህርቱን ተከታትሏል። ምሥራቅ ሐረርጌ ኮምቦልቻ ወረዳ ተወልዶ ያደገው ናስር  ፈረንሳይ ሀገር ሲማር ያየው እና ለሳምንት ያህል ጥናት ያደረገበትን አንድ ዋሻ ግን በጣም የማረከው ነበር። « ልዩ የሚያደርገው ሶዳ ስትሮ የተሰኘው ቀጭን ቱቦ የሚመሳስሉት ድንጋዮች ናቸው። ብርሃን ሳይገባ ራሱ በጣም ያምራል።  ውጭ ሀገር የተለያዩ የብርሃን መብራቶች ይጠቀማሉ።»

ድሮ ሰው ዋሻ ውስጥ ጥናት ሲያደርግ አብዷል ይባል ነበር

ናስር ድሮ ሰው ዋሻ ውስጥ ጥናት ሲያደርግ አብዷል ይባል ነበር አሁን ግን  እኔ ጥናት ማድረጌ ብዙ ነገር ቀይሯል ይላል።  ሁሉም ሰው የዋሻ ባለሞያ መሆን አይችልም የሚለው ናስር «ለሚያጨስ፣  አልኮል ለሚጠጣ ወይም ጭለማ ለሚፈራ ሰው የዋሻ ተመራማሪ መሆን ከባድ ነው» የሚለው ናስር ምክንያቱን ሲያስረዳ የኦክስጅን እጥረት ሊገጥም እንደሚችል እና በጣም እንደሚሞቅም ይናገራል።  ከዚህም ሌላ የተለያዩ እንስሶች ዋሻ ውስጥ ይገኛሉ ይላሉ፤ « ዘንዶዎች፣ የሌሊት ወፎች፣ ጅብ የመሳሰሉ ይገኛሉ» 
ስለሆነም በተግባር ለሚደረገው የዋሻ ምርምር  ወጣቶች ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው እና የናሽናል ጆግራፊ ዘገባዎችን እንዲከታተሉ ናስር ይመክራል። አራት ሰዎች ለምርምር ዋሻ ሲገቡ ሌሎች አራት ሰዎች ውጪ ሆነው እንደሚጠብቁ የገለፀልን ናስር   አዲስ ዋሻዎች ውስጥ አንዴ ሰዎች መግባት ሲጀምሩም እንስሶቹ ከዚያን ጊዜ በኋላ ከዋሻው እንደሚሸሹ ሊታዘብ ችሏል። 

የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ
የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድምስል N. Ahmed

ሶስቱ ሽልማቶች

ናስር በውጭ ሀገር ቆይታው ስለ ዋሻ በማጥናት የገንዘብ እና የእውቅና ተሸላሚ ነበር። ቢሆንም ባለፉት ሰባት ዓመታት ለሚያደርገው የዋሻ ምርምር እና ስለ ዋሻዎቹ በፃፈው መፅሀፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያገኛቸው ሶስት እውቅናዎች ይበልጥ ያኮሩታል። ናስር አብዛኛውን ጊዜውን ከቢሮ ይልቅ  ወደ ገጠራማው የሀገሩ አካባቢ በመጓዝ  ዋሻ  ፍለጋ እንደሚያሳልፍ ይናገራል። « ከዓመት ውስጥ ቢሮ የምቀመጠው ለሁለት ወራት ያህል ብቻ ቢሆን ነው» የሚለው ናስር ይህንን የወጣትነት ጊዜውን በስራ እና በሚወደው ነገር ማሳለፍ መቻሉ ያስደስተዋል። « ብዙ ሰው የእኔን ድምፅ ሲሰማ ትልው ሰው እመስለዋለሁ። እኔ ገና ወጣት ነኝ። ብዙ የምሰራቸው ነገሮች አሉ። ስለዚህ እንደፈለኩ መሄድ የምችለው ብቻዬን ስሆን ነው። ለግል ህይወት ገና ጊዜ አለኝ » ይላል። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከ328 ዋሻዎች በላይ ማግኘቱን የገለፀልን የዋሻ ተመራማሪ ናስር አህመድ።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ